ҽ

በኮንጎ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሰዎች በጎማ ከተማ ያሉትን ካምፖች ለቀው ሲወጡ በኮንጎ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሰዎች በጎማ ከተማ ያሉትን ካምፖች ለቀው ሲወጡ   (AFP or licensors)

በኮንጎ በተፈጠረ ግጭት ከ770 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ የጎማ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ሆስፒታሎች በመንግስት ሃይሎች እና በሩዋንዳ በሚደገፉ አማፂያን መካከል እየተደረገ በሚገኝ ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለማስተናገድ ከባድ ውጥረት ውስጥ እንደገቡ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትልቋ ምስራቃዊ ከተማ የሆነችው ጎማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ጨምሮ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን የሚኖሩባት ሲሆን፥ በኪቩ ግዛት ሥር የምትገኘውን ቡካቩ ከተማ ለመቆጣጠር ጉዞ ላይ በሚገኙ ኤም23 ተብለው በሚጠሩ ሚሊሻዎች እና በመንግስት ወታደሮች መካከል በሚደረግ ጦርነት ከባድ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የሚገኘው ሰሜን ኪቩ ለበርካታ ጊዜያት በጦርነት ከሚታመስ አከባቢዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሁድ ዕለት ባቀረቡት በመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ላይ እና ረቡዕ ዕለት በቀረበው ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ባደረጉት ንግግር በአከባቢው ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ሰው መጸለይ እንደሚገባ አደራ ብለዋል። ብጹእነታቸው ይሄንን ጥሪ ያሰሙት በጎማ ከተማ እና አካባቢው በተደረገው ግጭት ከ770 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ወደ 3000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተከትሎ ነው።

ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. የአማፂያኑ ጥቃት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአይን እማኞች እንደገለጹት በከተማው ጎዳናዎች ላይ በርካታ አስከሬኖች ወድቀው እንደሚታዩ እና የቀብር ስፍራዎች መጨናነቃቸውን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት የሟቾች ቁጥር በይፋ ከተመዘገበው ቁጥር በእጅጉ ሊበልጥ ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጥይት ወይም በፈንጂ ፍንዳታ ቆስለው ወደ ሆስፒታሎች የሚደርሱ ቁስለኞችን ለማከም የሚያስችል በቂ የሆነ የሰው ኃይል እና ቁሳቁስ ባለመኖሩ ምክንያት ከፍተኛ ችግር መከሰቱ የተነገረ ሲሆን፥ በርካቶች አንድ አልጋ ለሁለት ለመጋራት ሲገደዱ ሌሎች ደግሞ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ሆነው መሬት ላይ ተኝተው የህክምና ክትትል እየተጠባበቁ መሆኑ ተገልጿል።

በሽታዎች እንዳይስፋፉ ተሰግቷል
በርካታ ህዝብ በሚኖርበት የከተማው ክፍል እና በመላው ክልሉ ያለው የውሃ እና የመብራት እጥረት የበሽታ መስፋፋት ስጋትን እንደሚጨምር እና ከዚህም ጋር ተያይዞ አከባቢው ለኩፍኝ እና ለኮሌራ ወረርሽኝ ሊጋረጥ እንደሚችል ተነግሯል።

ኤም 23 ተብለው የሚጠሩት አማፂያን ጎረቤት ከሆነችው ሩዋንዳ ወደ 4,000 በሚጠጉ ወታደሮች እንደሚደገፉ የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ይህ አሃዝ በ2004 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ጎማን ተቆጣጥረው በነበረበት እና በዸም አቀፍ ጫና ምክንያት ከተማዋን ለቀው ለመውጣት በተገደዱበት ወቅት ከነበረው ቁጥር የሚበልጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በማዕድን የበለጸገውን የኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል ለመቆጣጠር ከሚፋለሙት ከ100 በላይ የታጠቁ ቡድኖች ውስጥ ኤም 23 በጣም ጠንካራ ቡድን እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን፥ ይህ አማፂ ቡድን ዘመናዊ የሆኑ የጦር መሳሪያ ክምችቶች እንዳሉት የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከ 2004ቱ ዓ.ም. ግጭት በተለየ መልኩ አማፅያኑ አሁን ላይ በፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ የምትመራው ሀገሪቱ የከሸፈች ሀገር መሆኗን በመግለጽ የኮንጎ ዋና ከተማ የሆነችው ኪንሻሳን ለመቆጣጠር እንዳቀዱ ይገልጻሉ።

ለአስርት ዓመታት ግጭት፣ መፈናቀል እና ስቃይ ያልተለያት ሃገር
የቅኝ አገዛዝ አሻራ ያለበት በኮንጎ የሚካሄደው ከአስርት ዓመታት በላይ የዘለቀው የጎሳ ግጭት የእርዳታ አቅርቦት ሰንሰለቱን በማወኩ የሰብዓዊ እርዳታ እጥረቶችን አስከትሎ ክፍተኛ ሰብአዊ ጥፋት አስድርሷል።

ከ 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በሰብአዊ ድጋፍ ሥራ ከህዝቡ ጎን የቆመው የጣሊያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰላም እንዲሰፍን ያቀረቡትን ጥሪ በማስተጋባት፣ በጎማ ከተማ ለሚካሄደው የአደጋ ጊዜ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሥራዎች ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ዩሮ እንደሚመድብ አስታውቋል።
 

04 Feb 2025, 14:18