ҽ

የሙሳዋህ የሴቶች ንቅናቄ አባላት የሙሳዋህ የሴቶች ንቅናቄ አባላት 

የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ለሙሳዋህ የሴቶች መብት ንቅናቄ እንደሚሰጥ ተነገረ

የጃፓኑ የኒዋኖ የሰላም ፋውንዴሽን ‘ሙሳዋህ’ ተብሎ የሚጠራውን የሴቶች ንቅናቄ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ሴቶችን ለማብቃት ላሳየው ቁርጠኝነት እና ሰላማዊ አብሮ የመኖር እሳቤን ለመፍጠር በሃይማኖቶች መካከል ውይይቶች እንዲጎለብቱ ላደረገው ጥረት እውቅና በመስጠት የ42ኛው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ተሸላሚ አድርጎ እንደመረጠው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኒዎኖ የሰላም ሽልማት ሰላምን ለማበረታታት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ በህይወት ላሉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በየዓመቱ የሚበረከት ሽልማት ሲሆን፥ 42ኛው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ሙስዋህ ተብሎ የሚታወቀው ድርጅት በሙስሊሙ ማህበረሰብ የቤተሰብ መዋቅር ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ሰብአዊ መብት ጥብቅና በመቆም ለፆታዊ ፍትህ እና እኩልነት ላበረከተው ዸም አቀፍ የሴቶች ንቅናቄ እንደሚሰጥ ተነግሯል።

ለፆታዊ እኩልነት መሟገት
የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ መሰረት በአረብኛ አቻ ትርጉሙ “እኩልነት” የሚል ፍቺ ያለውን የ ‘ሙሳዋህ’ ንቅናቄ ከታዋቂው የጃፓን የሰላም ሽልማት መርሆዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ “በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ውይይቶች መካከል የሴቶች መሪነት ለሰብአዊ መብት ጥበቃ እና በሰላም አብሮ ለመኖር” ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ መመረጡን ይፋ አድርጓል።

በ 2001 ዓ.ም. በማሌዥያዊቷ ዛይናህ አንዋር እና በኢራናዊቷ ዘይባ ሚር-ሆሴይኒ የተቋቋመው ሙሳዋህ በሙስሊም ሀገራት የሴቶች መብት ላይ አዎንታዊ ለውጦችን ለማበረታታት በሕግ እና በተግባር እውቅና ተሰጥቶት እየተተገበረ ያለውን ፆታዊ አድሏዊነትን ለመቃወም ጠበቆችን፣ ምሁራንን እና አክቲቪስቶችን በማሰባሰብ በርካታ ተግባራትን እንየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።

መስራቾቹ የንቅናቄውን አዕምሯዊ እና መንፈሳዊ መሰረት እንደጣሉ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ የተቋሙ አካሄድም በእምነት እና ሰብአዊ መብት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያረጋግጣሉ ተብሏል።

እንቅስቃሴው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በእስያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በሰሜኑ የዓለማችን ክፍል ያሉ ክልሎችን ጨምሮ ከ40 በላይ አገሮችን ያቀፈ ሰፊ የትስስር መረብ በመሆን በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ምክር ቤት ልዩ የምክክር አቋም ያለው ዸም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ እየሠራ ይገኛል።

በትምህርት እና በአመራር ልማት ላይ ያተኮረ ነው
የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ላይ የሙሳዋህ ንቅናቄ ዋነኛው ቁልፍ ገጽታ በትምህርት እና በአመራር ልማት ላይ ያተኮረ መሆኑን በማስታወስ፥ ትስስሩ በሙስሊም ማህበረሰብ አውድ ውስጥ የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማሳደግ ያለመ በርካታ የስልጠና መርሃ ግብሮችን እንዳዘጋጀ ገልጿል።

የተቋሙ እንቅስቃሴ አሳታፊ እና በሥነ-ምግባር የታነፀ የአመራር ሞዴሎችን በማፍራት ሴቶችን በፖሊሲዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር፣ አድሎአዊ አሰራርን ለመቃወም እና በሲቪክ እና በፖለቲካዊ ሂደቶች ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ግብዓቶች እንደሚያስታጥቃቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሙሳዋህ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም ከህግ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የማህበራዊ አገልግሎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሥርዓተ ፆታ ፍትህን የሚያበረታቱ የህግ አውጭ እና የፖሊሲ ለውጦችን ይደግፋል ተብሏል።

በፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን መከላከል
ሙሳዋህ ከህግ ጥብቅና ባሻገር ወርክሾፖችን፣ የስልጠና መርሃ ግብሮችን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን በማዘጋጀት ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በንቃት እየተቃወመ የሚገኝ ሲሆን፥ እነዚህ ውጥኖች ሴቶች ፆታዊ ጥቃትን እንዲቃወሙ እና እንዲከላከሉ በማበረታታት ብሎም ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ለመጠበቅ የሚረዳ ግብአቶችን እንዲሰበስቡ ይረዳል ተብሏል።

መግለጫው እንዳመላከተው ሙሳዋህ የቴክኖሎጂ እና የማህበራዊ ሚዲያን ሃይል በመገንዘብ ወጣቶች ዲጂታል መድረኮችን ለጥብቅና እና ለማህበራዊ ለውጥ እንዲጠቀሙ በማስተማር ተልዕኮው በትውልዶች ውስጥ ቀጣይነት እንዲኖረው እያረጋገጠ ይገኛል።

ሌላው የሙሳዋህ ጉልህ አስተዋፅዖ የሰነድ እና የእውቀት ስርጭት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ ድርጅቱ ከተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራዎች የተውጣጡ የሴቶች መብት ተሟጋቾችን ታሪክ እና አስተዋጾ በመዘርዘር ሰፊ ባለ ብዙ ቋንቋ ግብአቶችን አፍርቷል።

የኒዋኖ የሰላም ሽልማት
የቡድሂስት ፋውንዴሽን መስራች በሆነው ኒኪዮ ኒዋኖ ክብር በስሙ የተሰየመው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ዓላማው ዸም አቀፍ ሰላም እንዲሰፍን በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ትብብር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለሚያደርጉ ሰዎች እና ተቋማት እውቅና ለመስጠት እና ለማበረታታት በሚል ሽልማቱን እንደሚሰጥ ተገልጿል።

42ኛው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ሥነ ስርዓት ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፥ ለአሸናፊዎቹ ከሽልማቱ ሰርተፍኬት በተጨማሪ የሙሳዋህ ሜዳልያ እና የ20 ሚሊየን የን የገንዘብ ሽልማትን እንደሚያካትት አዘጋጅ ኮሚቴው ይፋ አድርጓል።
 

20 Feb 2025, 14:03