ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰውን ልጅ ምሉእነት ሊተካ የማይችል መሳሪያ ነው ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
አሳሳች የሆነው በመጀመሪያ ደረጃ ስሙ ነው። “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ወይም ሰው ሰራ አስተውሎት እየተባለ የሚጠራው ስሙ በብዙዎች ዘንድ ከሚነሳባቸው እና አሁንም እየተነሳባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች ውስጥ የጋራ ግንዛቤን መፍጠርን አለመቻሉ ነው።
በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጽ/ቤት እና የባህል እና የትምህርት ጽ/ቤት “አንቲኳ ኢት ኖቫ” (Antiqua et nova) በሚል ርዕስ ማክሰኞ ዕለት የተለቀቀው ማስታወሻ ሰነዱ በመጀመሪያ ደረጃ ሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያ መሣሪያ መሆኑን ያስታውሰናል፥ ይህም መተግበሪያ መሳሪያ ተግባሮችን ያከናውናል፥ ነገር ግን ማሰብ አይችልም፥ የማሰብ አቅምም የለውም። ስለዚህ የሰውን ባህሪያት ከዚህ መተግበሪያ መሳሪያ ጋር ማያያዝ አሳሳች ነው፥ ምክንያቱም እሱ በሎጂክ-የሒሳብ ቀመር ላይ ብቻ ላይ ተወስኖ የሚቀር “ማሽን” ነው። ይሄም ማለት ስለእውነታው የትርጓሜ ግንዛቤ፣ ወይም በትክክል የሚታወቅ ተፈጥሮአዊ አስተዋይነት እና የመፍጠር አቅም የለውም። ከዚህም በላይ ሥነ ምግባራዊ ማስተዋልን መተካት የማይችል ማሽን ነው። ከየትኛውም መገልገያ በላይ ለእውነት፣ ለመልካም እና ውብ ለሆነ ነገር ግልጽ የሆነ ፍላጎት የለውም። በአጭሩ እውነተኛ እና ጥልቅ የሆነ ሰብዓዊ ባህሪ የለውም ወይም ይጎለዋል።
በእርግጥ የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ ግለሰባዊ እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ማህበራዊ፣ ምክንያታዊ እና ተፅእኖ ፈጣሪ ነው። የሚኖረውም በሰውየው መተኪያ በሌለው የሰውነት አካል አማካይነት ቀጣይነት ባለው ግንኙነት ነው። በመሆኑም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅን የማሰብ ችሎታን የሚረዳ ወይም የሚያሟላ መሳሪያ ብቻ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋል ያለበት እንጂ የሰው ልጅን ልዩ ምልዓት በምንም ዓይነት ሁኔታ መተካት አይችልም።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ምንም እንኳን ለምርምር እድገት አስተዋጽዖ ቢኖረውም ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ሃላፊነት የሌለበት “ማሽን” ሆኖ ይቀጥላል፣ ካልሆነም በፈበረኩት እና በሚጠቀሙበት ሰዎች እጅ ይቀራል።
በዚህም ምክንያት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ተመስርተው ውሳኔ የሚያደርጉ ሰዎች ለመረጡት ምርጫ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉ እና የዚህ መሳሪያ አጠቃቀም ተጠያቂነት በእያንዳንዱ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ሊኖር እንደሚችል መገንዘቡ አስፈላጊ መሆኑን ማክሰኞ ዕለት የወጣው አዲሱ ሰነድ አመላክቷል።
ሁለቱም በሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ዘዴዎች እና አተገባበሮች የሰውን ክብር እና የጋራ ጥቅም ማክበራቸውን እና ማሳደጋቸው ስለመቻላቸው መገምገም አለባቸው። ይህ ግምገማ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አጠቃቀምን ህጋዊነት ወይም በሌላ መንገድ ለመለየት መሰረታዊ የሥነ-ምግባር መስፈርትን ያካትታል።
ሌላው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሥነ-ምግባር ግምገማ መስፈርት የሰው ልጅ ከአካባቢው እና ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት አወንታዊ ገፅታዎች በመተግበር የግለሰቦችን እና ማህበረሰቦችን ገንቢ ትስስር ለመፍጠር እና ለጋራ ጥቅም የጋራ ሃላፊነትን ለማጎልበት ያለውን አቅም እንደሚመለከት ማስታወሻ ሰነዱ ይጠቁማል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንደገለፁት እነዚህን ግቦች ከዳር ለማድረስ ከመረጃና ከዕውቀት ክምችት በዘለለ እውነተኛውን “ልባዊ ጥበብ” ለማግኘት መጣር ያስፈልጋል፥ በዚህም አግባብ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በአግባቡ መጠቀም የሰው ልጅ የተሻለ እንዲሆን ይረዳል።
ማስታወሻው ሰነዱ ከዚህ አንፃር ለቴክኖሎጂ መገዛት እንደሌለብን በማመልከት፥ ቴክኖሎጂው አዳዲስ የመገለል ስልቶችን እና የማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ስለሚፈጥር ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የሰውን ጉልበት ቀስ በቀስ ለመተካት እንዳንጠቀም በመምከር፥ ከዚህ ይልቅ ለሰው ልጅ የሚደረግ እንክብካቤን ለማሻሻል እንዲሁም አገልግሎቶችን እና የሰዎች ግንኙነትን ለማሻሻልና ለማጎልበት ብቻ መተግበሪያ መሳሪያውን እንድንጠቀም መክረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ውስብስብ እውነታዎችን ለመረዳት የሚረዳ እና እውነትን ፍለጋ ውስጥ የምናረገውን ጥረት የሚያግዝ መሳሪያ መሆን እንዳለበትም ጭምር ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካይነት የሚሰራጩ ማጭበርበሮችን መከላከል የዘርፉ ባለሙያዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ሰው ጥረት ይጠይቃል።
እንዲሁም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንደ ጉልበት ብዝበዛ ወይም የሰዎችን ነፃነት ለመገደብ የሚውል መሳሪያ ሆኖ እንዳያገለግል መከላከል አለብን። በብዙዎች ኪሳራ ጥቂቶችን ለመጥቀም፣ ወይም እንደ ማህበራዊ ቁጥጥር አይነት እና ሰዎችን ወደ ውስን የመረጃ ስብስብ ለመቀነስ እንዳያገለግል መጠንቀቅ ይገባናል።
ከዚህም ባለፈ በጦርነት መስክ የሰውን ህይወት ለማጥፋት የሚያገለግል መሳሪያ ሆኖ ሥራ ላይ እንዳይውል መፍቀድ ዬለብንም። እንደ አለመታደል ሆኖ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አከባቢ በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ እንደታየው በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመራ መሳሪያ ያስከተለውን አስከፊ ውድመት እያስተዋልን እንገኛለን።