ҽ

በሮም የሚገኝ የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ተከፈተ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመዝሙረ ዳዊት ምዕ. 122:1-2 ላይ፥ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። ኢየሩሳሌም ሆይ፣ እግሮቻችን በደጆችሽ ውስጥ ቆመዋል” የሚለውን የመዝሙረኛውን ቃል በማስታወስ የቀንደ መለከት ድምጽ በተሰማበት ሥነ-ሥርዓት የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር የመክፍቻ ሥነ-ሥርዓት እሑድ ታኅሳስ 27/2017 ዓ. ም. የመሩት የባዚሊካው ሊቀ ካኅናት ካርዲናል ጄምስ ሚካኤል ሃርቬይ እንደ ነበሩ ታውቋል።

በሮም የሚገኙ የአራቱ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች በሮች እነርሱም የቅዱስ ጴጥሮስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር፣
የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር፣ የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር እና በሮም ውስጥ የሚገኝ የረቢቢያ ማረሚያ ቤት ቅዱስ በር ለመክፈት በወጣው መርሃ ግብር መሠረት እሑድ ታኅሳስ 27/2017 ዓ. ም. የተከፈተው የመጨረሻው በር የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር እንደ ነበር ታውቋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ምዕመናን የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ንዋያተ ቅዱሳት ወደሚገኝበት ባዚሊካ ከመግባታቸው በፊት ፊታቸውን ወደ ቅዱስ መስቀል በማዞር፥ ሞትን እና ኃጢአትን የሚያሸንፍ የሕይወት ምልክት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግቢያ እና ተስፋ መሆኑን እርግጠኝነት የሚገልጹ ቃላትን ደግመዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መከፈት
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት ከተሰቃየበት ቦታ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ርቆ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ የቅዱስ በር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በጸሎት ተፈጽሟል። የባዚሊካ ቅዱስ በር በጸሎት ሥነ-ሥርዓት የከፈቱት የባዚሊካው ሊቀ ካኅናት ካርዲናል ጄምስ ሃርቬይ በቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ጉልህ የሆኑ ክስተቶችን በሚያሳዩ ምስሎች ከነሐስ የተሠራውን በር በጸሎት መንፈስ ከከፈቱት በኋላ የበሩን መከፈት የባዚሊካው ደወሎች አብስረዋል።

የኢዮቤልዩ መዝሙር እየተዘመረ ብፁዕ ካርዲናል ሃርቬይ በሩን የተሻገሩ ሲሆን ቀጥሎም የቅዱስ ጳውሎስ ገዳማዊ ማኅበረሰብ አባላትም በዑደት ወደ ባዚሊካው ከገቡ በኋላ ወደ መንበረ ታቦቱ አምርተዋል። የባዚሊካው ሊቀ ካኅናት ካርዲናል ጄምስ ሃርቬይ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ጋር በመሆን ወደ ባዚሊካው ማዕከላዊ ሥፍራ ደርሰዋል። ቀጥሎ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከ2,800 በላይ ምዕመናን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንዶች ተገኝተዋል። 

የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ
የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ
በሮም በሚገኝ የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ የተፈጸመ የቅዱስ በር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት

ደስታ እና ተስፋ
መስዋዕተ ቅዳሴን የተካፈሉት ምዕመናን ከዮሐንስ ወንጌል የተወሰደውን እና የእግዚአብሔርን መገለጥ የሚያበስር፥ “በመካከላችን ሊሆን መጣ” የሚለውን ክፍል አዳምጠዋል። ብፁዕ ካርዲናል ሃርቬይ የቅዱስ በር መከፈትን በማስመልከት ባሰሙት ቃለ-ምእዳን፥ “የበሩ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ይህን ያህል ቀላል ቢመስልም ነገር ግን ቀስቃሽ ተግባር መሆኑን ገልጸው፥ “የባዚሊካውን በር በታላቅ ደስታ እና ተስፋ በምሳሌያዊ መንገድ ተሻግረናል” ካሉ በኋላ የቅዱስ ዓመት ሁለት ቁልፍ ቃላት፥ ደስታ እና ተስፋ በመጥቀስው፥ የምንደሰተውም አዳኛችን እና ተስፋችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተወለደልን ነው” ብለዋል።  

ይቅርታ እና ምህረት
“ደስታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላለው የመቤዠት ስጦታ ትክክለኛው ስሜት ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሃርቬይ፥ በዚህ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን እና በእግዚአብሔር ሕዝቦች የተፈጸመውን ሥነ-ሥርዓት አንድ ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል። የብርሃነ ልደቱ ሰሞን ደስታ ዘንድሮ በኢዮቤልዩ በዓል መታጀቡን የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ ይቅርታን የሚያስገኝ ይህ የቅዱስ ዓመት ጉዞ ሰዎች ለሚወስዱት እርምጃ ሁሉ መሪ እንደሆነ አስረድተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ሃርቬይ በስብከታቸው፥ “የቅዱስ በር መከፈት ክርስቶስ በሥጋ በመገለጡ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው በተከፈተው የድነት ምስጢር የቤተ ክርስቲያን አባላት በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርሳቸው እንዲታረቁ የሚጠራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ቅዱስ በርን በእምነት መሻገር ማለት ወደ ምህረት እና ወደ ይቅርታ ጊዜ መግባት ማለት ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሃርቬይ፥ ማንንም የማያሳፍር ይህ የተስፋ መንገድ ለእያንዳንዱ ሴት እና ወንድ ክፍት ነው” ብለው፥ በድህረ-ወረርሽኙ ወቅት፣ በአደጋ፣ በጦርነት እና በተለያዩ ቀውሶች ምክንያት ለቆሰለው ዓለማችን ተስፋ ያስፈልገናል!” ሲሉ በመግለጽ፥ ምንም እንኳን ተስፋ ከወደፊቱ ጊዜ ጋር የተቆራኘ ቢሆንም በዚህ ጊዜ እንለማመደዋለን” በማለት አስረድተዋል።

የተስፋ ነጋዲያን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለታዳሚዎቻቸው በጠቅላላት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ላይ የተናገሩትን ሲያስታውሱ፥ ተስፋ ባዶ ቃል እንዳልሆነ ወይም ነገሮች በጎ እንዲሆኑ የሚል የኛ ግልጽ ያልሆነ ምኞት እንዳልሆነ ገልጸው፥ “ይልቁንም ተስፋ የተረጋገጠ እና በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ተስፋ አንድ ሰው ነገሮች እስኪፈጸሙለት ድረስ ብቻ የሚጠብቅበት ጊዜ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው አፅንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት ተስፋ “ነገሮች እንዲፈጠሩ የሚረዳ እጅግ ንቁ በጎነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. የሚከበረው የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት እንደ ሌሎች ቅዱስ ዓመታት መንፈሳዊ ንጋዲያን እንድንሆን ይጠይቀናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሃርቬይ ቃለ-ምዕዳናቸው ሲያጠቃልሉ፥ “በዚህ ዓለም ውስጥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን እያወጀ ለሁለት ሺህ ዓመታት ሲጓዝ የኖረ ማኅበረሰብ አካል መሆንን የሚያካትት፥ እያንዳንዱ ነጋዲያን የእምነት ፈለግ በመከተል መንፈሳዊ ጉዞ እንዲያደርግ ቤተ ክርስቲያን ትጋብዛለች” ብለው፥ በዚህ የእምነት ጉዞ ላይ በማያሳዝን ተስፋ ጸንተን መቆየት እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ይሁን” በማለት ቃለ-ም ዕዳናቸውን በጸሎት ደምድመዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር መክፈቻ ሙሉ ሥነ-ሥርዓት
18 January 2025, 16:15