ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከህመማቸው እያገገሙ እንደሆነ እና ትኩሳታቸውም እንደቀነሰ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰኞ አመሻሹ ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የጤና ሁኔታ አስመልክቶ የወጣው መግለጫው ‘ቅዱስ አባታችን የነበረባቸው የትኩሳት መጠን እንደቀነሰላቸው እና ዶክተሮቻቸው ባዘዙላቸው የህክምና ሂደት መሰረት እየታከሙ እንደሆነ ገልጿል።
የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽህፈት ቤት ሰኞ አመሻሽ ላይ ለጋዜጠኞች ይፋ ባደረገው መልዕክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. አርብ ዕለት የብሮንካይተስ ወይም የመተንፈሻ አካል ሕመም ስለተሰማቸው እና አጠቃላይ የሕክምና ምርመራ ለማድረግ በሮም ከተማ ወደ ሚገኘው ጂሜሊ በመባል ወደ ሚታወቀው ሆስፒታል መግባታቸው ተገልጿል።
ጽህፈት ቤቱ አክሎም ቅዱስ አባታችን አሁን ያሉበት ሁኔታ የተረጋጋ እንደሆነ በመግለጽ፥ ሰኞ ጥዋት ላይ ቅዱስ ቁርባንን እንደተቀበሉ፣ ከዚያም የተወሰኑ ጳጳሳዊ ስራዎችን እንዳከናወኑ እና አንዳንድ ፅሁፎችን ማንበብ እንደጀመሩ አብራርቷል።
ጋዜጣዊ መግለጫው በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ ከገቡበት ወቅት ጀምሮ እየደረሳቸው ባሉት በርካታ የፍቅር እና የአብሮነት መልዕክቶች ልባቸው በደስታ እንደተነካ መግለፃቸውን በማስታወስ፣ ልባዊ ፍቅራቸውን በተለያዩ ምስሎች እና የመልካም ምኞት መልዕክቶች ለገለጹላቸው ሰዎች በተለይም ደግሞ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች እና ሰራተኞች ላደረጉላቸው እንክብካቤ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ ለእነዚህ ሁሉ እንደሚጸልዩላቸው እና እነሱም እንዲጸልዩላቸው መጠየቃቸውን ገልጿል።
ከሰኞ ዕለት ቀደም ብሎ የጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤቱ ሳምንታዊው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በቅዱስ አባታችን ህክምና ምክንያት እንደተሰረዘ ማስታወቁ ይታወሳል።