ҽ

ቫቲካን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የሕፃናት መብቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አዘጋጅታለች ቫቲካን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የሕፃናት መብቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አዘጋጅታለች  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለሕጻናት የሚውል ሐዋርያዊ ምክር እንደሚጽፉ አስታወቁ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ጉባኤ መርሃግብርን ሲዘጉ ባደረጉት ንግግር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ህፃናት ‘በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ወደፊት እንደምንራመድ ለማወቅ ይመለከቱናል’ በማለት አበክረው ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. የህፃናት መብቶች የሚታወሱበት ቀን ሆኖ እንዲከበር የተሰጠ ቀን ሲሆን፥ ቫቲካን የመጀመርያውን በሕፃናት መብት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች በተገኙበት በጳጳሳዊ የመኖሪያ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ተናጋሪዎች መሰረታዊ የሰብአዊ መብት የሌላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ዓለም አቀፍ ቀውስ ላይ ለመወያየት የተሰባሰቡ ሲሆን፥ በጉባዔው ወቅት ከተሰሙ ዐበይት መልዕክቶች ውስጥ “ከሕፃናት ሕይወት በላይ የበለጠ ዋጋ የሚሰጠው ነገር የለም” የሚል መልዕክት እንደነበር ተነግሯል።

ለሕጻናት የሚውል ሐዋርያዊ ምክር
ድህነት፣ ጦርነት፣ የትምህርት እጦት እና የጉልበት ብዝበዛ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ልጆች በየቦታው ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው እና ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸው ይታወቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጉባኤው አዳራሹ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ህፃናት ላይ በሚደርሱ እውነታዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ለማድረግ ለተሰበሰቡ ለሁሉም ተሳታፊዎች እና ተናጋሪዎች ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቀላሉ ከሚታዩበት ቦታ ላይ ሆነው ባደረጉት ንግግር ጉባኤውን “ቤተ ሙከራ ወይም ላቦራቶሪ” ብለው የገለጹ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው የቅድስት ምድር ጠባቂ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙትን አባባል በመድገም “በዓለም ዙሪያ ያሉ ህፃናት ‘በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ወደፊት እንደምንሄድ ለማወቅ ሲሉ ይመለከቱናል’ በማለት ለተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሀሳባቸውን ያጠቃለሉት ለህፃናት የሚሆን ብሎም ይህ ቁርጠኝነት ቀጣይነት እንዲኖረው እና በመላው ቤተክርስትያን በኩል ሃሳቡን ለማስፋፋት እንዲቻል ሐዋርያዊ ምክር ለመጻፍ እንዳሰቡ በማመላከት ነው።

ማንኛውም ልጅ የእኛን ጥበቃ የማግኘት መብት አለው
ከተደረጉት ሰባት ያክል የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የያዙ የፓነል ውይይቶች መካከል በዘመናዊው ዓለም ያለው የልጆች መብት አጠባበቅ እና የትምህርት ተደራሽነት እስከ ምግብ እና የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት ጉዳዮችን በማንሳት ሰፊ ውይይት እንደተደረገ ተገልጿል።

በዘመናዊው ዓለም የሕፃናት መብትን አስመልክቶ ከተነሱት የመጀመሪያዎቹ መልዕክቶች ውስጥ የዮርዳኖስ ንግሥት ራኒያ አል አብዱላህ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር እያንዳንዱን ልጅ መንከባከብ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “እያንዳንዱ ህጻን የእኛን ጥበቃ እና እንክብካቤ እኩል የማግኘት መብት አለው፣ ምክንያቱም ዓለም ለህጻናት የገባው ቃል ይህ ነውና” በማለት አበክረው ገልጸዋል።

ንግስቲቱ በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት አስደንጋጭ የሆነ መረጃን በማስታወስ፥ በተጠናው ጥናት መሰረት በአከባቢው ከሚገኙት 96 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት በማንኛውም ሰዓት መሞታቸው እንደማይቀር ሆኖ እንደሚሰማቸው፣ እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ መሞት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ገልጸው፥ “የእኛ የሰብአዊነት ሥነ ልቦና ወደዚህ ደረጃ እንዲመጣ እንዴት ፈቀድን?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ንግሥት አል አብዱላህ አክለውም የሰው ልጅ በትጋት ጥረት ካደረገ ብቻ ነው መጪው ዓለም የተሻለ እና ውብ ራዕይ ሊኖረው የሚችለው ብለዋል።

ገደል አፋፍ ላይ ያለ ፕላኔት
የስነ-ምህዳር ውድመት ስጋትን በማስጠንቀቅ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት አል ጎር በበኩላቸው ‘ይህ በምድራችን ላይ በሚኖሩ ህፃናት ላይ የጫንነው ሸክም ነው’ በማለት የሥነ ምህዳር ውድመት ምድራችንን በገደል አፋፍ ላይ ያለች ፕላኔት እንዳደረጋት ከጠቀሱ በኋላ፣ ‘አይቶ እንዳላዩ መሆን’ ብዙዎች የዓለም ሙቀት መጨመርን፣ የሙቀት አማቂ ጋዞች እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶችን ማየት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የአየር ንብረት እውነታ ፕሮጀክት መስራች እና ፕሬዝዳንት የሆኑት አል ጎር ከዚህም በተጨማሪ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የአሁኑ ትውልድ ሳይሆን መጪው ትውልድ እንደሆነም አስታውሰዋል።

ከችግሮቹ በስተጀርባ ያለውን ችግር ለይቶ ማወቅ
የ ጂ.ኬ.ኤስ.ዲ. ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ፕሬዝዳንት የሆኑት ካሚል ጊሪቢ በበኩላቸው ህፃናት የዓለም ውበት መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ፥ ‘በልጆች ላይ ለሚደርሰው ረሃብ እና ኢፍትሃዊነት ብቻ መፍትሄ ከመፈለግ ባሻገር የችግሩን ምንጭ ማወቅ አለብን’ በማለት የተከራከሩ ሲሆን፥ “ከችግሩ በስተጀርባ ያለውን ችግር እና ምክንያቱን መፈለግ አለብን” በማለት አጽንዖት በመስጠት አሳስበዋል።

አቶ ካሚል አክለውም በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ፣ ብሎም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከቃላት በዘለለ ይህን የመሪዎች ጉባኤ ከሌሎች የተለየ እንዲሆን፥ እንዲሁም ይህ ጉባኤ ካለቀ በኋላ ህጻናትን የመርዳት ጥሪን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የጠየቁ ሲሆን፥ ሁሉንም በአንድ ላይ ሰብስቦ፣ የሚያምሩ ንግግሮችን ከማዳመጥ ይልቅ የመሪዎች ጉባኤ አባላት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበው፣ ‘ዛሬ ሁላችንም ከዚህ ጉባኤ ስንወጣ ተጨባጭ የሆኑ ተግባራትን እንደምናደርግ ተስፋ አደርጋለሁ’ ብለዋል።

የተግባር ጥሪ
በጉባዔው መገባደጃ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከሌሎች ተናጋሪዎች ጋር በመሆን የህጻናትን መብት መጠበቅ እና እንክብካቤን በሚመለከት ስምንት መርሆችን የያዘ ሰነድ ላይ የፈረሙ ሲሆን፥ በዚህ የተግባር እና ፍትሃዊ የሆነ መጪው ጊዜን የመፍጠር ጥሪ ምንም እንኳን የመሪዎች ጉባኤው ዛሬ ቢጠናቀቅም ሁሉም ህጻን በጣም መሠረታዊ የሆኑትን የሰብአዊ መብቶች እስኪያገኝ ድረስ ተልዕኮው ይቀጥላል ተብሏል።
 

05 Feb 2025, 13:07