ҽ

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ የኢየሱስን መወለድ በቅድሚያ የመሰከሩት ትሁት እና ድሃ የሆኑ ሰዎች ናቸው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰብያ አዳራሽ ለሚገኙ ምዕመናን በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በየካቲት 05/2017 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን የምንገኝበትን የኢዩቤሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ የልጅነት ጊዜ" በሚል ዐብይ አርእስት ጀምረው ከነበረው አስተምህሮ በመቀጠል "እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና" (ሉቃስ 2፡11) በሚል ንዑስ አርእስት ዙሪያ ላይ የኢየሱስ ልደት እና የእረኞች ጉብኝት በተመለከተ ባደረጉት የክፍል አምስት አስተምህሮ "የኢየሱስን መወለድ በቅድሚያ የመሰከሩት ትሁት እና ድሃ የሆኑ ሰዎች ናቸው" ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል

"መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ" (ሉቃስ 2፡10-11)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ!

በዚህ በያዝነው የኢዩቤሊዩ አመት ሂደት ውስጥ ተስፋችን በሆነው በኢየሱስ ላይ ጀምረነው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ኢየሱስ በቤተልሔም ስለተወለደበት ሁኔታ እናሰላስላለን።

የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ተጓዥ ጓዳችን ሆኖ በታሪካችን ውስጥ ገባ፣ እናም ገና በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ መጓዝ ይጀምራል። ወንጌላዊው ሉቃስ ኢየሱስ ጋና በማሕጸን ውስጥ ሳለ ከናዝሬት ወደ ዘካርያስና ወደ ኤልሳቤጥ ቤት ሄደ፣ ከዚያም በእርግዝና መጨረሻ ወቅት ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም ለሕዝብ ቆጠራ ሄደ ይለናል። ማርያምና ​​ዮሴፍ ወደተወለደበት ወደ ንጉሥ ዳዊት ከተማ እንዲሄዱ ተገደዱ። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የልዑል እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ ራሱን እንደማንኛውም ዜጋ እንዲቆጠር ማለትም እንዲመዘገብ ይፈቅዳል። የምድር ሁሉ ገዥ ነኝ ብሎ ለሚያስበው አውግስጦስ ቄሳር ንጉሠ ነገሥት ትእዛዝ ተገዛ።

ወንጌላዊው ሉቃስ የኢየሱስን ልደት “በትክክል በተያዘለት ጊዜ” እና “በተጠቆመ መልክዓ ምድራዊ (ጂኦግራፊያዊ) መቼት” ውስጥ አስቀምጦታል፣ ስለዚህም “ሁለንተናዊው እና ተጨባጭ የሆኑ ነገሮች እርስ በርስ ይነካካሉ” (BENEDICT XVI፣ The Infancy Narratives፣ 2012፣ 77)። ስለዚህም ወደ ታሪክ የሚመጣውን እና የአለምን አወቃቀሮች የማያፈርስ፣ ነገር ግን እነሱን ሊያበራላቸው እና ከውስጥ ሊፈጥራቸው የሚፈልገውን አምላክ ትህትና ያሳየናል።

ቤተ ልሔም ማለት "የዳቦ ቤት" ማለት ነው። በዚያም የማርያም የመውለጃዋ ቀን የሚፈጸምበት ቦታ ሆነ፣ በዚያም ኢየሱስ ተወለደ፣ የዓለምን ረሃብ ለማርካት የሚችል እንጀራ ከሰማይ ወረደ (ዮሐ. 6፡51)። መልአኩ ገብርኤል የመሲሐዊውን ንጉሥ መወለድ በታላቅ ምልክት ተናግሮ ነበር፡- “እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም”  ( ሉቃስ 1፡31-33 )።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተወለደው ለንጉሥ ፈጽሞ በማይታሰብበት እና በማይገመትበት መንገድ ነው። በእርግጥም “በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው" (ሉቃስ 2፡6-7)። የእግዚአብሔር ልጅ የተወለደው በንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ሳይሆን ከቤት ጀርባ፣ እንስሳት በምያድሩበት ጋጣ ውስጥ ነበር።

ቅዱስ ሉቃስ ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ ዓለም የሚመጣው በሚያስተጋባ አዋጅ እንዳልሆነ ያሳየናል፣ በጩኸት አይገለጥም፣ ነገር ግን በትህትና ጉዞውን ይጀምራል። እናም የዚህ ክስተት የመጀመሪያ ምስክሮች እነማን ናቸው? እረኞች ናቸው፡ ትንሽዬ ባህል ብቻ ያላቸው፣  ከእንስሳት ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ያላቸው መጥፎ እንደሆኑ ተደርገው የሚታሰቡ፣ ከህብረተሰቡ ተገልለው የሚኖሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ለሕዝቡ የሚገለጥበትን ሥራ ይለማመዳሉ (ዘፍ. 48:15፤ 49:24፤ መዝ 23:1፤ 80:2፤ ኢሳ 40:11)። አምላክ በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ አስደሳች የሆነውን “አትፍሩ፤  እነሆ፥ ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስና ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ" በማለት ይነግራቸዋል።

ከመሲሑ ጋር የሚገናኙበት ቦታ በግርግም ውስጥ ነው። በእርግጥ፣ ከእንዲህ ዓይነት ጥበቃ በኋላ፣ “የዓለም አዳኝ፣ ሁሉም ነገር በእርሱ በተፈጠረው (ቆላ. 1፡16)፣ ለእርሱ በዚህ ምድር ሥፍራ ወይም ቦታ ይጠፋል" (Benedict XVI፣ The Infancy Narratives፣ 2012፣ 80) የሆነው ይከሰታል። እረኞቹ ስለዚህ በጣም ትሑት በሆነ ቦታ፣ ለእንስሳት ብቻ በተፈቀደ ቦታ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ መወለዱን እና አዳኛቸው፣ እረኛቸው ይሆንላቸው ዘንድ እንደተወለደ ተማሩ። ይህ ዜና ልባቸውን ለመደነቅ፣ ለምስጋና እና ለደስታ አዋጅ ይከፍታል። ‘ከሌሎች ብዙ ሰዎች በተለየ፣ በብዙ ነገሮች የተጠመዱ፣ እረኞች ከሁሉም በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመዳን ስጦታ ለማየት የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ። ትሑት እና ድሆች ናቸው ቃል የነበረውን ከዚያን በኋላ ደግሞ ሥጋ የለበሰውን እርሱን በቅድምያ የሚሳለሙት" ነርሱ እረኞች ናቸው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ እኛም እንደ እረኞች በእግዚአብሔር ፊት መደነቅ እና ማመስገን የምንችል፥ የሰጠንን ስጦታዎች፣ ፀጋዎች፣ ጥሪያችንን እና ባልንጀራዎቻችንን እንድንከባከብ ጸጋን እንለምን። አለምን ሊያድስ እና ህይወታችንን ሊለውጥ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ተስፋ ባለው እቅዱ የሚመጣውን የህፃኑ እግዚአብሄርን ልዩ ጥንካሬ  ማስተዋል እንድንችል ጌታ ጸጋውን እንዲሰጠን እንለምነው።

12 Feb 2025, 13:08

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >