ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ዓለማችን ተስፋ እንዲኖረው የወንጌል ደስታን ለሌሎች ማካፈል ይገባል” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሰዎች በደስታ እና በሐዘን ውስጥ ወድሚገኙበት ዓለም ውስጥ መሄድን በፍጹም አትፍሩ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የወንጌልን ደስታ እና ተስፋ ለሌሎች እንድናውጅ ለሚገፋፋን ለመንፈስ ቅዱስ ራስን አሳልፎ መስጠት ይገባል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በፈረንሳይ የወንጌል ስርጭትን ለማነሳስት ይህን ጠንካራ የማበረታቻ ምክራቸውን የለገሡት፥ በርካታ የፈረንሳይ ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ ሚስዮናዊ ተነሳሽነቶችን ለሚያስተባብሩ ሃምሳ አባላት ዓርብ ጥር 2/2017 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር እንደ ነበር ታውቋል።
ቡድኑ በየዓመቱ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት የሚቆይ ዓመታዊ ዝግጅት በማስተባበር በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ለጸሎት እና የእግዚአብሔርን ቃል ለመካፈል በመሰብሰብ በዛሬው ዓለም ወንጌልን በተሻለ መንገድ ማወጅ በሚቻልበት ዘዴ ላይ እንደሚወያይ ታውቋል።
ዓለም ክርስቲያናዊ የተስፋ መልዕክትን በእጅጉ ይፈልጋል!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለልዑካን ቡድኑ ባደረጉት ንግግር፥ የሚስዮናዊ ኮንግሬስ አባላት ለወንጌል አገልግሎት ላሳዩት ታማኝ ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ይህ የወንጌል አገልግሎት ክርስቲያናዊ መልዕክት እጅግ ለሚያስፈልገው ዓለማችን የብርሃን እና የተስፋ ምንጭ ነው” ብለዋል።
ዘንድሮ በፈረንሳይ-በበርሲ ከተማ የሚካሄደው ስብሰባ ከኢዮቤልዩ ተስፋ ጋር የተገናኘ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ደስታ፣ ተስፋ እና ተልዕኮ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በማስረዳት ጊዜያዊ ጉጉት ብቻ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግል ከተገናኘን በኋላ ወደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ዘንድ የሚመራን መሆኑን አስረድተዋል።
ስለዚህም “የተስፋ ንጋዲያን መሆን ማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብሮ መጓዝ፣ ወደ ሌሎች ዘንድ ለመሄድ ድፍረትን ማግኘት እና በወንጌል ላይ የተመሠረተ ህያው ቃል ለዓለም በማቅረብ የሚያጽናኑ እና አዳዲስ መንገዶችን የሚከፍቱ ቃላትን መስጠት ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ክርስቶስ ከሌሎች ጋር መካፈል ያለብን ተስፋ ነው!
ዓለማችን በግጭት፣ በፍትሕ መጓደል እና በሚከፋፍሉ የግለኝነት ፈተናዎች ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ክርስቶስ ተስፋችን ነው!” የሚለው ክርስቲያናዊ እርግጠኝነት ከሌሎች ጋር መጋራት ያለብን የብርሃን ስጦታ ነው” በማለት አጽንዖትን ሰጥተው፥ የኮንግሬሱ ሚስዮን መሪዎች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ለተልዕኮ ጥሪ በድፍረት ምላሽ እንዲሰጡ አሳስበዋል። “ይህ ማለት ከወደቁበት ውርደት መውጣት እና ግራ መጋባትን ከመፍጠር ጋር ሊያያዝ ቢችልም ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስን ብልሃት ይሰጥናል” ብለዋል።
የመጀመሪያዎቹ የተስፋ ነጋዲያን ወጣቶችን ማነሳሳት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኮንግሬሱ ሚስዮን አስተባባሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በተለይም የመጀመሪያዎቹ የተስፋ ነጋዲያን ወጣቶች በእምነት እንዲያድጉ በመርዳት፣ ደፋር ምርጫ በማድረግ ራሳቸውን የኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክተኛ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ በማበረታታት እንዲያግዟቸው አደራ ብለዋል።
“ወንድማማችነት የሰፈነበት ዓለምን ለመገንባት ውስጣዊ ድፍረት እንዲኖራቸው በማድረግ በቤተ ሰቦቻቸው፣ በትምህርት ቤቶች እና በሥራ ቦታዎች የተስፋ ልጆች እንዲሆኑ፣ በአረጋውያን እና በወጣቶች መካከል ግንኙነትን እንዲያበጁ መርዳት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አንድነትን ማሳደግ ለዓለም ጠንካራ ምስክርነት ነው!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መደምደሚያ፥ በኮንግሬሱ ሚሲዮን መካከል አንድነት መጉደል እንደሌለበት በማሳሰብ፥ “አንድነትን ማሳደግ ለዓለም ጠንካራ ምስክርነት እንደሆነ፥ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን የሚገልጽ የሕያው ፍቅር ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“አንድነት እርስ በርሳችን ባለን ፍቅር የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ዓለም የሚያውቅበት ጠንካራ ምስክርነት ስለሆነ እርስ በርሳችሁ በመረዳዳት እና በመደጋገፍ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣችሁ ፍሬዎች አብራችሁ ደስ ይበላችሁ” ብለዋል።
በማጠቃለያቸውም በኅዳር ወር 2018 ዓ. ም. የሚያካሂዱት 11ኛው ስብሰባቸው በፈረንሳይ ውስጥ ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የደስታ፣ የመለወጥ እና የመታደስ ጊዜ እንዲሆን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል።