ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ወድቀው በቀኝ ክንዳቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ እለት ጥር 07/2017 ዓ.ም ጠዋት በቫቲካን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ማርታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ወድቀው እንደ ነበረ የተዘገበ ሲሆን ነገር ግን ምንም ዓይነት ስብራት እንዳልደረሰባቸው የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ቢሮ ዘግቧል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
መግለጫው አክሎ እንደ ገለጸው ከሆነ ቅዱስነታቸው "በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ወድቀዋል፣ በመውደቃቸው ምክንያት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቀኝ ክንዳቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት የአጥንት ስብራት አላጋጠማቸውም" ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ የቅዱስነታቸው “እጅ ለጥንቃቄ ሲባል እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል” ሲል ገልጿል።
ምንም እንኳን ክስተቱ ቢፈጠርም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንቱ ውስጥ ለእርሳቸው የታቀዱትን ዝግጅቶች መታደም መቀጠላቸው የተገለጸ ሲሆን በዋቢነትም የዓለም የምግብ ዋስትና ኮሚቴ ሊቀ መንበር ኖሲፎ ናኡስካ-ዣን ጄዚሌን ጨምሮ ከተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ጋር የምያደርጉትን ግንኙነት መቀጠላቸው ተዘግቧል።
17 January 2025, 14:13