ሰው እግዚአብሔርን ለመቀበል ያለው ችሎታ
ሰው እግዚአብሔርን የሚናፍቀው ለምንድነው?
እግዚአብሔር ራሱ ሰውን በራሱ አምሳል ስለፈጠረ፣ እርሱን የሚያይበትን ናፍቆት ብዙ ጊዜ ችላ ቢልም እንኳ እግዚአብሔር ሰውን ወደራሱ መሳቡን ከቶ አያቋርጥም፤ ምክንያቱም ያለማቋረጥ የሚፈልገውን የእውነትና የደስታ ሙላት የሚያገኘውና በእርሱም የሚኖርበት በእግዚአብሔር ብቻ ነውና። ስለዚህ፣ በተፈጥሮም ሆነ በመንፈሳዊ ጥሪ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ሊኖረው የሚችል መንፈሳዊ ፍጡር ነው። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ቅርብና ወሳኝ ትስስር ለሰው ልጅ መሠረታዊ ክብሩን ያጎናጽፈዋል።
በሰው አእምሮ ብቻ እግዚአብሔርን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
ከፍጥረት ማለትም ከዓለምና ከሰው ልጅ መፈጠር ተነሥቶ ሰው በአእምሮው ብቻ እግዚአብሔር የዓለም
መጀመሪያና መጨረሻ፣ ቸርነቱ የበዛ፣ ወሰን የሌለው እውነትና ውበት መሆኑን በእርግጠኛነት ሊያውቅ ይችላል።
የአእምሮ ብርሃን ብቻ የእግዚአብሔርን ምስጢር ለማወቅ ያስችላል?
ሰው በአእምሮው ብቻ እግዚአብሔርን ለማወቅ ብዙ ችግሮች ያጋጥሙታል። በመሠረቱ፣ ሰው በራሱ ወደ መለኮታዊ ምስጢር መግባት አይችልም። ለዚህም ነው ከዕውቀቱ በላይ የሆኑትን ነገሮች ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ከሰው አእምሮ በላይ ያልሆኑትን መንፈሳዊና ግብረገባዊ እውነታዎችንም ለማወቅ የእግዚአብሔር የመገለጥ ብርሃን የሚያስፈልገው። ያን ጊዜ የሰው ዘር አሁን ባለበት ሁኔታ እንኳ በቀላሉ፣ በእርግጠኝነትና ያለ ምንም ስሕተት በሁሉም ዘንድ ሊታወቁ ይችላሉ።
ስለ እግዚአብሔር መናገር የምንችለው እንዴት ነው?
በውስን ደረጃም ቢሆን የእግዚአብሔር ወሰን የሌለው ፍጹምና ነፀብራቅ የሆኑትን የሰውንና የሌሎች ፍጥረታትን ፍጽምና መነሻ አድርገን ብንወስድ ከሰዎች ሁሉ ጋር ስለእግዚአብሔር መነጋገር እንችላለን። ይሁን እንጂ፣ በሐሳብ የታጠረና ያልተሟላ እስከሆነ ድረስ ንግግራችንን ያለማቋረጥ ማጥራትና ወሰን የሌለውን የእግዚአብሔር ምስጢር ሙሉ በሙሉ መግለጽ እንደማንችል መገንዘብ ይኖርብናል።
እግዚአብሔር ለሰው ምን ይገልጣል?
እግዚአብሔር በቸርነቱና በጥበቡ ራሱን ይገልጣል። ራሱንና ከጥንት ጀምሮ በክርስቶስ የወሰነውን የፍቅር ዕቅድን በሥራም በቃላትም ይገልጣል። በዚህ ዕቅድ መሠረት ሰዎች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ እንደተገኙ “ልጆች” በአንድያ በእግዚአብሔር ልጅ መለኮታዊ ሕይወት ይካፈላሉ።
የእግዚአብሔር መገለጥ የመጀመሪያ ደረጃዎች ምንድናቸው?
ከመጀመሪያ አንሥቶ፣ እግዚአብሔር ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ራሱን ገለጠ፣ ከእርሱ ጋር ህብረት እንዲኖራቸውም ጠራቸው። እነርሱ በኃጢአት ከወደቁም በኋላ፣ መገለጡን አላቋረጠም፣ ለዘሮቻቸውም ሁሉ ደኀንነትን እንደሚሰጣቸው የተስፋ ቃል ገባ። ከውሃ ጥፋት በኋላ ከኖህ ጋር እንዲሁም በራሱና በሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ቃል ኪዳን አቆመ።
የእግዚአብሔር መገለጥ ቀጣይ ደረጃዎች ምንድናቸው?
እግዚአብሔር አብራምን መረጠ፣ ከአገሩም ጠራው፣ “የብዙ አሕዛብ አባት አደረገው” (ዘፍ. 17፡5) በእርሱም በኩል “የምድርን አሕዛብ ሁሉ” እንደሚባርክ ቃል ገባለት (ዘፍ. 12፡3)። የአብርሃም ዘሮች ለአበው የተገባውን መለኮታዊ ቃል መጋቢዎች ሆኑ። እግዚአበሐር እስራኤልን የራሱ ሕዝብ አድርጎ መረጣቸው፣ ከእነርሱም ጋር በሲና ተራራ ላይ ቃል ኪዳን አቆመ፣ በሙሴም አማካይነት ሕጉን ሰጣቸው። ነቢያት ስለ ሕዝቡ መሠረታዊ መዳንና ሁሉንም ሕዝቦች በአዲስና ዘላለማዊ ቃል ክዳን ውስጥ ስለሚያካትተው ደኀንነት ሰበኩ። ከሕዝበ እሰራአልና ከንጉሥ ዳዊት ቤት ኢየሱስ መስሕ ተወለደ።
የእግዚአብሔር መገለጥ የመጨረሻና ወሳኝ ደረጃ ምንድነው?
የእግዚአብሔር መገለጥ የመጨረሻና ወሳኝ ደረጃ የፈጸመው ሥጋ በሆነው ቃሉ፣ መካከለኛና የመገለጥ ሙላት በሆነው በኢየስስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ሰው የሆነ የእግዚአበሐር አንድያ ልጅ ነው፣ የአብ ፍጹምና የመጨረሻ ቃል ነው። የዚህን ቁምነገር የቤተክርስትያን እምነት በዘመናት ሂደት ቀስ በቀስ የሚገነዘበው ቢሆንም በወልድ መምጣትና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተነሣ የእግዚአብሔር መገለጥ አሁን ሙሉ በሙሉ ተፈጽሞአል።
“ልጁን፣ አንድያና የመጨረሻ ቃሉን፣ ለእኛ በመስጠት እግዚአበሐር ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ በዚህ አንድያ ቃሉ ተናገረን፤ ስለዚህ ሌላ የሚናገረው ነገር የለም” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል)።
የግል መገለጦች ዋጋ ምንድነው?
የእምነት ሀብት አካል ባይሆኑም፣ የግል ራእዮች ወደ ክርስቶስ እስከመሩን ድረስ ሰውን በእምነት እንዲኖር ሊረዱ ይችላሉ። እነዚህነ የመሰሉ የግል ራእዮችን የመመርመር ኃላፊነት ያለበት የቤተክርስያን የላይ አመራር ወሳኝ መገለጥ የሆነውን ክርስቶስን እንልቃለን ወይም እናርማለን የሚሉትን የግል ራእዮች አይቀበልም።
NJͭ፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ይፋ ካደረጉት ከዋናው ከላቲን መጽሐፍ ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 27-78 ላይ ተጨምቆ የተወሰደ።
አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን