ҽ

ከቡርኪናፋሶ የተፈናቀሉ ሴቶች ከቡርኪናፋሶ የተፈናቀሉ ሴቶች  (AFP or licensors)

በቡርኪናፋሶ የሚገኙ ክርስቲያኖች ለአሸባሪዎች ጥቃት እና ሽፍቶች መጋለጣቸው ተነገረ

በምዕራብ ቡርኪናፋሶ በደረሰ የሽብር ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት እርዳታ የሚያሰባስበው የካቶሊክ የእርዳታ ተቋም ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጥር ወር መገባደጃ ላይ ከ200 በላይ የሚሆኑ አሸባሪዎች በምዕራብ ቡርኪናፋሶ በሚገኙ ሶስት መንደሮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር በትንሹ 6 ክርስቲያኖችን ጨምሮ 26 ሰዎችን መግደላቸው ይታወሳል። እነዚህ አሸባሪዎች የበርካታ ነዋሪዎችን ቤት በማቃጠላቸው ምክንያት የአከባቢው ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በተከሰቱ ተጨማሪ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

በጥቃቱ አባታቸውን እና ሌሎች በርካታ የቤተሰብ አባላትን ያጡት ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢን ኒድ’ ተብሎ የሚታወቀው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ቤተ ክርስቲያናት እርዳታ የሚያሰባስበው የካቶሊክ በጎ አድራጊ ድርጅት ፕሮጄክት አጋር የሆኑት አባ ዣን ፒየር ኬይታ የሽብር ጥቃቱን ዜና ይፋ አድርገዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በምዕራብ ቡርኪናፋሶ ባንዋ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ታንሲላ ሃገረ ስብከት ውስጥ ሲሆን፥ ደብሩ 37 መንደሮችን እንደሚያጠቃልል እና ከአጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ አንድ ሦስተኛው ክርስቲያን እንደሆነም ተነግሯል።

አባ ዣን ፒየር ጥቃቱ ለደረሰባቸው ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ “እባካችሁ ሁሉም ሰው ሰላም ፈጣሪ ይሆን ዘንድ አምላክ ልቦና እንዲሰጣቸው ጸልዩ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አባ ዣን ፒየር ባቀረቡት የጸሎት ጥሪ ላይ በአሸባሪነት ተግባሩ የተጎዱትን ሰዎች በማስታወስ “ጸሎታችን በዓለም ዙሪያ የአሸባሪዎች ጥቃት ለደረሰባቸው ሰለባዎች ሁሉ ነው፥ ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ” ብለዋል።

ካቴኪስቶች ተገድለዋል
የመጀመርያው ጥቃት በታንሲላ በተፈፀመበት በዚያው ቀን፣ በምዕራባዊ የቡርኪናፋሶ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሙሆውን ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው የዴዱጉ ሀገረ ስብከት የመጡ ሁለት ካቴኪስቶች ከካቴኪስት የሥልጠና መርሃ ግብር ሲመለሱ በዘራፊዎች ተገድለዋል።

የዘራፊዎቹ ቡድን ጥቃት በተፈፀመበት ወቅት ከኦዋካራ ቁምስና የመጡ አራት ካቴኪስቶች በሁለት ሞተር ሳይክሎች አብረው ሲጓዙ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻቸው እንደነገሯቸው የካቶሊክ የእርዳታ ተቋም የዘገበ ሲሆን፥ በመጀመሪያው ሞተር ሳይክል ላይ የነበሩት ሁለቱ ካቴኪስቶች ወደ ጫካው ማምለጥ ቢችሉም ሁለቱ ባልደረቦቻቸው ግን ተገድለው ተገኝተዋል።

የቦንዶኩይ ከተማ አካባቢ ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሉት አካባቢው ዘረፋ ለመፈፀም አሸባሪ መስለው የሚታዩ ሽፍቶች የሚንቀሳቀሱበት ስፍራ መሆኑን ገልጸው፥ ባለስልጣኑ እንዳሉት የካቴኪስቶች ግድያ በቅርብ ወራት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ድጋፍ ለምትሻ ቤተክርስትያን እርዳታ የሚያሰባስበው ተቋም በመጨረሻም እንደገለጸው በአካባቢው በክርስቲያኖች ላይ እየተካሄደ ያለው ከባድ ጥቃት በእጅጉ እንደሚያሳስበው በመግለጽ፥ ለኦዋካራ ቁምስና ማህበረሰብ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለቡርኪናፋሶ ሰላም ጸሎት እንዲደረግ ጥሪውን ካቀረበ በኋላ፥ ሀገሪቱ በፀጥታ እጦት እየተሰቃየች እንደሆነ እና በክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለው ስደት መቀጠሉን ጠቁሟል።
 

19 Feb 2025, 14:37