የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ በዕዳ ስረዛ ዘመቻ ላይ የፋይናንስ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጥሪ አቀረበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከዓለም ኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ፍትህ እና ከፋይናንሺያል መረጋጋት ጋር በተያያዘ በተለይም ባልተረጋጋ የእዳ ጫና ውስጥ በሚገኙ ታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት ዕዳ ስረዛ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ ይነገራል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰሜን እና በደቡብ ዓለም መካከል ያለውን የስነ-ምህዳር ዕዳ በመገንዘብ የድሃ ሃገራት የውጭ ዕዳዎች እንዲሰረዙ’ ያደረጉትን የትብብር ጥሪ ተከትሎ በተጀመረው የ2025 የዕዳ ስረዛ ዘመቻ ኢዮቤልዩ ላይ የተገኙት የምስራቅ አፍሪካ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ሊቀመንበር ብጹእ አቡነ ቻርልስ ሳምፓ ካሶንዴ “የዕዳ ስረዛ ዘመቻው ሊራዘም ይችላል” ብለዋል።
“ሀገሮቻችንን ያስጨነቀውን የውጭ ሃገራት እዳ አዙሪት ለመከላከል የታለመ ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ ማሻሻያዎችን እንፈልጋለን” ያሉት የዛምቢያዋ ሶልዌዚ ከተማ ጳጳስ የሆኑት ካሶንዴ፥ እኛ ፍትሃዊነትን እና እኩልነትን የሚያረጋግጡ እንዲሁም ኃላፊነት የተሞላባቸው የመበደር እና የማበደር ተግባራትን እናበረታታለን ካሉ በኋላ የማገገሚያ ስልቶችን በአስቸኳይ ማጤን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ወደ ዘላቂ እፎይታ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት የሚወስዱ መንገዶች
የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በኬንያ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ንግግር ያደረጉት ዛምቢያዊው ጳጳስ የዕዳ ስረዛ ድርድሮች የፋይናንስ ሸክሞችን በማቃለል ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ያሉ ሲሆን፥ ሀገራት እየጨመረ በሚሄደው የዕዳ ጫና ጋር እየታገሉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ዕዳዎችን መልሶ ማጤን የመክፈያ ውሎችን ለማስተካከል፣ የፋይናንስ ጫናን ለመቀነስ እና ዘላቂ የእድገት መንገድን ለመፍጠር ውጤታማ መፍትሄ እንደሚሰጥ አስታውሰዋል።
“የክፍያ ሸክሙን ለማቃለል እና ዘላቂነትን የሚያረጋግጡ ፍትሃዊ የዓለም አቀፍ የብድር ውሎችን ለማድረግ ትርጉም ያለው የዕዳ ማሻሻያ ድርድር ላይ መሳተፍ አለብን” ያሉት ብጹእ አቡነ ካሶንዴ፥ ከዚህም በተጨማሪ ሀገሮቻችንን ወደ እድገት እና የማገገም ጎዳና ለመመለስ ውጤታማ የታክስ ማሻሻያ በማድረግ የሀገር ውስጥ ገቢን ማጠናከር ቁልፍ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።
የኢዮቤልዩ መንፈስን መቀበል
ብጹእ አቡነ ካሶንዴ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 25 ከቁጥር 8 እስከ 13 ላይ የተጠቀሰውን ነፃነትን፣ ዕዳ ስረዛን እና ፍትሕ ላይ ባተኮረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት በመነሳት የኢዮቤልዩ ዓመት በብሉይ ኪዳን ፅንሰ-ሀሳብ በመነሳሳት በመንፈስ የመታደስ፣ የይቅርታ እና የዕርቅ ጊዜ እንደሆነ አስታውሰው፥ ‘ታሪካዊውን እና የሞራል ግዴታ የሆነውን የኢዮቤልዩ መንፈስ በደስታ እንቀበል’ ሲሉ መልዕክታችውን አስተላልፈዋል።
ብጹእ አቡነ ካሶንዴ አክለውም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ባህል የመነጨው ኢዮቤልዩ ጊዜውን የዋጀ የዕዳ ስረዛ እንዲደረግ እንዲሁም ይቅርታ እና የኢኮኖሚ ሚዛን እንዲኖር ጥሪውን ያቀርባል ካሉ በኋላ፥ ከዚህም ባለፈ የተስፋ ብርሃን፣ የመታደስ እና የነጻነት ቃል ኪዳን፣ እንዲሁም ለረጅም ጊዜያት ለዘለቀው መዋቅራዊ አለመመጣጠን መፍትሄ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ዕዳን ይቅር ማለት ትልቅ የሞራል ኃላፊነት እንደሆነ ያስተላለፉትን መልዕክት በማስተጋባት፣ “ዕዳ ድህነትን ሲያስፋፋ፣ ኢፍትሃዊነትን ሲያጎላ እና የኢኮኖሚ እድገትን ሲያዳክም በተለይ 'የተስፋ ተጓዦች’ በሚል መሪ ቃል እያከበርን በምንገኘው የ 2025 ኢዮቤልዩ ዓመት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንገደዳለን” ካሉ በኋላ ይህ ጊዜ ከድርጅታዊ ትርፍ እና ከአበዳሪ ሀገራት የበላይነት ይልቅ ሰብአዊ ክብርን በማስቀደም የፋይናንስ ስርዓታችንን እንደገና እንድናጤነው ያስገድደናል ሲሉ አሳስበዋል።
እዳ ስረዛን አስመልክቶ የኢዮቤልዩ አበርክቶ
የኢዮቤልዩ መርህ ሁል ጊዜ የእዳ ቅነሳን በሚደግፉ እንቅስቃሴዎች ላይ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች የዕዳ ስረዛን በመደገፍ ብዙ ሃገራት እውነተኛ የገንዘብ እፎይታ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም የማይበገር ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ልማት እንዲሰፍን አድርገዋል።
ይሄንንም በማስመልከት የ 2000 ኢዮቤልዩ ዘመቻን ያስታወሱት ብጹእ አቡነ ካሶንዴ፣ አንዳንድ በጣም ከፍተኛ ዕዳ ለነበረባቸው ሃገራት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ እንዲሰረዝ ማድረጉን በማስታወስ፥ በዚህም ምክንያት ሃገራቱ ገንዘባቸውን ለጤና አጠባበቅ፣ ለትምህርት እና የመሰረተ ልማትን ለመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ የህዝብ አገልግሎቶች እንዲያውሉ አድርጓል ብለዋል።
ሆኖም ግን የተገኘው እፎይታ የአፍሪካ ሃገራትን ለተደጋጋሚ የእዳ ቀውሶች የሚዳርገውን በዓለም አቀፍ የፋይናንሺያል ሥርዓት ውስጥ ያሉትን የአሰራር ጉድለቶች ለማስተካከል በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ “ይህንን ጊዜ እንደ ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ በጋራ ለመቆም እንደ ትልቅ አጋጣሚ እንቀበለው” በማለት አጠቃለዋል።